"በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ሥፍራ ነው፡፡ እኔ አላውቅም ነበር"፡፡ ዘፍ 28፣16-28

እጅግ ደካማ የሆንኩ ብሆን፣ ያየሁትን መመስከር ለሚሰማና እዝነ ልቦናው (የልቦናው ጆሮ) ለሚሰማለት ሁሉ መንገር፣ መመስከር ተገቢ ስለሆነ እንጂ በኔ በደካማው የሚነገር አልነበረም ።  ምንም እንኳ  ለመፃፍ እየተነሳሁ ሰሚ በሌለበት መድከሙ ተስፋ እያስቆረጠኝ ብተወውም የኋላ ኋላ ግን እኔም እራሴ የዚህ ትውልድ አካል ሆኘ ይህን ማሰቤ ስህተት መሆኑን ስለተረዳሁ አንደገና ለመፃፍ ተነሳሁ።

ብዙ ጊዜ የኛ ትውልድ ስለሀገሩ እና ሃይማኖቱ የሚነገረውን ነገር ሁሉ ተጠራጣሪ በመሆን  እና ስለራሱ ሀገር ሌላው ባዕድ (ነጭ) እንዲመሰክርለት ፤ማረጋገጫ እንዲሰጠው ካልሆነ በቀር ሊቀበለው አይሻም። በተለይ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በኩል ያሉትን ታሪኮች፣ እውቀቶች እና ጥበቦች ትውልዱ መቀለጃ ካደረጋቸው ውሎ አድሯል። እውነተኛውን ከፈጣሪው  ያገኘውን የአምልኮት ስርዓት እና አካሄድ ይዞ ሰይጣንን ድል እየነሳ ለዘመናት ያቆየውን ኢትዮጵያዊ እውነት የተሸከምከው እኮ በግ ሳይሆን ውሻ ነው ብለው በሐሰት መስክረው  የተሸከመውን በግ አስወርደው በግ ነው ያሉትን ውሻ አሸክመውት እርሱም ከመዘብዘቡ ብዛት ውሻውን በግ ነው ብሎ ሲሞግት እነሆ ዘመናትን ተሻገረ። ዛሬ ባእዳን ውሻ ነው ያሉትን በግ አርደው ለመብላት ሲሽቀዳደሙ የኛ ትውልድ ግን ባእዳን ያሸከሙትን ውሻ ተሽክሞ በግ እኮ ነው እያለ ሲዞር ማየት፣ ያሳዝናል በውነት፣ ልብም ይሰብራል።  በዚህም ምክንያት ትውልዱ፤ ባእዳን ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያን ከረገጡባት ጊዜ አንስቶ፤ ያሉትን ሁሉ እየተቀበለ የራሱን እውነት፣ ፀጋና፣በረከት የሆነውን "እርኩስ" ብሎ የባእዳንን የሰይጣን አምልኮ ፣ ተንኮል እና ተልዕኮ  "ቅዱስ" በማለት ላይ ይገኛል። በኦሪት ዘመን ለአምላኩ ለእግዚአብሔር ሲሰዋ የነበረውን ሕዝብ፤ አሕዛብ ነበርኩኝ ብሎ እንዲያስብ ፣ እንዲያምን ፣ ከኦሪቱ ወደ ክርስትና ሲሸጋገር በ34 አመተ ምህረት ዓለም በተቀበለው መፅሐፍ ላይ ተመስክሮ እያለ፣ ወንጌልን በአራቱም መአዘናት ሀገሪቱን ዙረው ያስተማሩ የወንጌል አርበኛች የነበሩባት ሃገር ስትሆን ፤ ወንጌል ያልተሰበከልህ፣ ቃሉንም የማታውቅ ነህ ሲሉት ባእዳን እናንተ ካላችሁ እሽ ብሎ እነርሱ እንዳሉት እና እንዳሳዩት እግዚአብሔርን ላምልክ እያለ እንደዶሮ ሲጭር፣ እንደአውሬ ሲጮህ፣ ሲዘል እና ሲያጓራ ሲታይ ልብን በሃዘን ያደማል። ብቻ ብዘረዝረው ፣ቢዘረዘር፣ ቢዘረዘር አያልቅም። ከስነ-ተፈጥሮአችን ጀምሮ የሰው ዘር መገኛ፣ የዳበረ ባህል እና  የደረጀ ቤተ መዘክር የሆነችቱን ኢትዮጵያ ባእዳን ሊያጠፏት ቢጥሩም እርሷ ግን አለች እስከዛሬ። እውነት ያሸንፋል እና! አሁንም እናያለን ባእዳን እና ትውልዱ ውሻ ነው ያሉት እውነት መገለጡ ደግሞ አይቀርም። ለቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ ያለቀሱላት የቅዱሳኖቿ እንባና ፀሎት እንዲሁ አይቀርም። ያንጊዜ በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ሥፍራ ነው፡፡ እኔ አላውቅም ነበር ይላል ዓለም።



አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ተቃዋሚዎች

ብዙ ውሽት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ። ክፍል 2 '' መንግስት''