ብዙ ውሽት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ። ክፍል 2 '' መንግስት''

የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ETV) ባለፍት ቅርብ ጊዜያት በእስላማዊ አክራሪነት ጠንቅ ላይ ያተኮረ 'ጥናታዊ ፊልም' በተከታታይ ሲያቀርብልን ፤ መንግስትም ደረስኩበት ያለውን ምስጢር ሲያጋልጥና ሕዝቡን ከእልቂት ለመከላከል ቀን ከሌት በትጋት እየሰራ መሆኑን ሲነገረን ሰነበተ ። መልካም ይህም ባልከፋ። ምንም እንኳ ከበርካታ አመትታት በፊት ቤተክርስቲያን በአክራሪ እስልምና አራማጆች በኩል የሚደርስባትን ጥቃት ለመንግስት እያሳወቀች ብትቆይም ፤ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ የነበረው መንግስት ፣ አሁን ነገሩ ወደርሱ ህልውና ሲመጣ እና ሲያነጣጥር 'ጉዳዩ ፣ ጉዳዬ ነው ፣ እኔንም ያገባኛል' ብሎ ይሄው እያራገበው ይገኛል። ቤተክርስቲያን ሲቃጠል፣ ምእመናን እና ካህናት በግፍ ሲታረዱ ፤ 'አላየሁም ፣ አልሰማሁም' ያለው መንግሥት አሁን አሁን እኔንም ያገባኛል ማለት ጀምሯል። ኢ.ቴ.ቪ. ያስተላለፋቸው በአክራሪነት ላይ ያተኮሩት እነዚህን ፊልሞች ሁሉኑንም ለመከታተል ሞክሬያለሁ። እንደመንግስት ማድረግ የሚገባውን እያደረገ ነው ስል ለራሴ ህሊናዬን ሞግቻለሁ። መንግስት ሀገር የሚመራ ፣ ኃላፊነት የሚሰማው አካል አድርጌ እረዳው ስለነበር በጥናታዊ ፊልሙ ውስጥ የቀረቡትን ስህተቶች ጭምር ስህተት ቢሆኑም በበጎ ጎኑ ለመቀበል ህሊናዬን ሳስጨንቅ  ነበር። ነገር ግን ተደጋግመው የሚወጡት የዚህ ጥናታዊ ፊልም ዘገባዎች ስህተቱ ሆነ ተብሎ የታቀደበት ስህተት እንጂ እንዳጋጣሚ የሆነ እንዳልነበረ እያረጋገጡልኝ መጡ። ታሪክን ካለማወቅ የመጣ ሳይሆን እያወቁ የሚያጠፉ መሆኑን እየተረዳሁ መጣሁ። በመጨረሻም ግልጽ በሆነ ሁኔታ አቅጣጫን የማስቀየር ስራ እየሰሩ እንደሆነ ግልጽ ሆነልኝ።ይህም እንዲህ ነው።

ባለፍት የኢ.ቴ.ቪ  ተከታታይ 'ጥናታዊ ፊልሞች' ሰለ አክራሪነት የሚያውቁትን፣ የሚገምቱትን፣ የደረሱበትን፣ የሰሙትን፣ ያስቀባጠሩትን ወ.ዘ.ተ ሰብስበው አቀበሉን። በዚህ መሃል ግን አብሮ ሳይነሳ የማያልፍ አንድ ነገር ነበረ። እርሱም የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ናት። እርሷንም በመጠኑ ወረፍ እያደረጓት ያልፉ ነበር። ከላይ እንደገለጽኩት ይህንን ሁኔታ ክፋት ይኖረዋል ብዬ  ለማሰብ ተቸግሬ ነበር። ለመንግስት ካለኝ ትልቅ ቦታና ከማንኛውም የፖለቲካ አስተሳሰብ ነጻ በመሆኔ፣ ተንኮል ይኖረዋል ብዬ ለማሰብ ተቸግሬ ነበር። ነገር ግን 'ጥናታዊ ፊልሙ' በቀጠለ ቁጥር ይህችው ቤተክርስቲያን ስሟ እየተብጠለጠለ ፣ ታሪኳ ጥላሸት እየተቀባ ይቀርብልን ጀመር። በመጨረሻም የእስልምና ጠላት እንደነበረችና መንግስት እስልምናን እንደታደገው የሙስሊሞችም ባለዉለተኛ እንደሆነ በመግለጽ መልእክቱን በግልጽ አስቀመጠ።  አንድምታውም ሲጠቀለል 'ስትገልህ፣ ስታሳድድህ የኖረች ቤተክርስቲያን ናትና አቅጣጫህን አዙር እኔ አንተን የታደኩ ባለውለታህ ነኝ' የሚል ሆነ። መንግስት ይህን ካለ በኋላ ለታሪክ ማጣቀሻነት አጼዎቹን አነሳ። ምን አለ አሁን ሚዛን ደፍቶ እነ ግራኝም ቢነሱ አልኩ በልቤ። አንደው ሌላው ቢቀር ያነሳቸውን አጼዎቹን እንኳ ታሪካቸውን በትከክል ቢያቀርብ ምን አለበት። እንዲህማ አይሆንም። ምክንያቱም ትክክለኛ ታሪካችው እኮ እስልምናን አይጨቁንም! ስለዚህ መበላሸት አለበት። አንድ ጥያቄ ግን አለኝ። ማንም የመሰለውን ታሪክ ለፈለገው አላማ ሲናገር ሕዝቡን አላዋቂ አድርገው ቆጥረውት ይሆን? እንደው 94 ሚሊዮን ሕዝብ መናቅ ይሆን? ሲጀመር እኒህ አጼዎች ሊወደሱ ሊመሰገኑ ይገባቸዋል። በመንግስትም በሙስልሞችም በኩል። በታሪክ እንኳ እኛ ኢትዮጵያውያን በዓለም እራሱ እንደሚመሰክረው በ615 የነብዮ መሐመድ ተከታዮች በእርግጠኝነት ጥገኝነት ሊያገኙባት እንደሚችሉ አምነው የመጡባት ሀገር ኢትዮጵያ ናት። ንጉሱም የክርስትና እምነት ተከታይ ነበረ። ስለዚህ መንገስቱም ክርስቲያናዊ መንግስት ነበረ። የከበረ እና የተመሰገነ የሆነው ይህ ንጉስ ስሙ እንኳን በአግባቡ ተጠርቶ አያውቅም። እንዲያውም አጼዎቹ ጋር ተደምሮ ሲጥላላ  ነው የምናየው። እንግዲህ ከታሪክ እንደምንረዳው ኢትዮጵያ የክርስቲያን ንጉስ በነበራት ሰዓት እስልምና ከነመፈጠሩ እንኳ አይታወቅም ነበረ። ከዚያም እስልምና ቀስ በቀስ ኢትዮጵያ ውስጥ መስፋፋት ጀመረ። በእንግድነት የመጡት ሰዎች እምነቱን አስፋፉ የሚል የታሪ ማስረጃ በበኩሌ አላገኝሁም። እስልምና እየተስፋፋ የመጣው ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በሌሎች አለማት በግዳጅ ውይም በጦርነት ነው። ሲጀምር በምስራቅ ኢትዮጵያ (ሐረር) ፣ በመቀጠል በጥንት ጊዜ በነበራት ጠረፋማ አካባቢዎች እና በሶማሊያ በኩል በኃይል እየተንሰራፋ እንደመጣ ይታወቃል። ይህም ከኢትዮጵያ በሰሜን አቅጣጫ የሚገኙ ክርስቲያኖች ይህንን ኃይል ለመመከት እንደተታገሉ የታሪክ ማህደራት ይገልጻሉ። እንዲህ  እንዲህ  እያለ ነው እንግዲህ እስልምና ቀስ  በቀስ በሁለት እግሩ ኢትዮጵያ ውስጥ መቆም የጀመረው። ታዲያ በዚህ የእስልምና የልጅነት ጊዜ እስልምና በጥቂት የኢትዮጵያ ጠረፋማ ስፍራዎች ብቻ ተወስኖ ቆይቷል። በወቀቱ የነበሩ ክርስቲያናዊ ነገሥታትም በኃይል የመጣባቸውን ሲመክቱና አጸፋውን  ሲመልሱ ጊዜያቸውን አሳልፈዋል። በወቅቱ የነበሩት ነገስታት እና ሰፊው ሕዝብ ክርስቲያን ሰለነበር ቤተ ክህነት አና ቤተ ምልክና (ቤተመንግስት) በመናበብ ያገለግሉ ነበር። እንዲህ አይነቱ ምንግሥት ለረጅም ጊዜ ኢትዮጵያን ሲያስተዳድር ኖሯል። እንዲህ አይነቱ መንግስት ለክርስቲያኖች ያደላል አንኳ አንዳይባል፣ ዓለም ገና እስልምና ምን ይሁን ምን ሳይረዳ ፣ ሳያውቅ የነብዮ መሐመድን ተከታዮች 'ተልኮአችሁ ምንድን ነው? ወዴት ናችሁ? ቁጭ በሉ፣ ተነሱ፣ ወዲያ በሉ፣ ወድህ በሉ ሳይል እጁን ዘርግቶ ተቀብሏቸዋል። የቅርቡን አጼ እንኳ ብናነሳ የሃይማኖትን እኩልነት በሚገልጽ መልኩ ሃይማኖት የግል ነው ሀገር ግን የጋራ ነው በሚለው መርሃቸው ነው የምናውቃቸው። 

ሌላው የደነቀኝ ነገር 'ጥናታዊ ፊልሙ' የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ አንበሳ መስቀል ይዞ የሚታይበትን እያንቋሸሸና እያናናቀ ሲናገር መስማቴ ነው። ሲጀመር ሰንደቅ አላማውን ያገኘነው ከኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ነው (encyclopedia ተመልከት)። ቤተክርስቲያን ደግሞ ይህንን ሰንደቅ አላማ ለሀገሪቷ መለያ ስታደርግ እና ሃይማኖታዊ ምስጢሩን ስትሰራ እስልምና  አልነበረም (ከኖህ ቀስተደመና የመጣ ነውና)። የክርስቲያን ነገስታት ደግሞ ሲነግሱ የእየሱስ ክርስቶስ ምሳሌ የሆነውን አንበሳ፣ የመዳን ምልክት የሆነውን መስቀል ይዞ በሰንደቅ አላማው ላይ እንዲታይ ተደረገ። ዛሬ የሙስሊም ሃገራት የሆኑት ጨረቃና ኮከብ ባንዲራቸው ላይ እንደሚያደርጉት ፤ የክርስቲያን ሃገራት ለምሳሌ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ፊንላንድ፣ እና ዴንማርክ (ምንም እንኳ በስም ብቻ ክርስቲያን ቢባሉም አና  የማያምነው ቢበዛም) ሰንደቅአላማቸው ግን የመዳን ምልክት መስቀል እንዳለው እስከዛሬ ድረስ አለ። ታዲያ ዛሬ አክራሪ እስልምና መንግስትን አስጨነቀው ተብሎ እነዚያ የከበሩ አና የተመሰገኑ ደጋግ ክርስቲያናዊ ነገስታት በዘመናቸው ሰንደቅ አላማቸው ላይ የመስቀል ምልክት ለምን አደረጉ ብሎ መራገም በሙሉ ጨረቃ ላይ ኮከብ ቀርጾ የብሔር፣ ብሄረሰቦችን እኩልነት ያመለክታል ብሎ የሚያፌዘውን አካል ማንነት እና ለማን እየወገነ መሆኑን በግልጽ ያስረዳል።

ከዚህም በተጨማሪ እስልምናን እና ክርስትናን ለማነጻጸር የተጠቀሙበት አካሄድ ሃይማኖታዊ መሰረት የሌለው የመንግስት ጥራዝ ነጠቅ ግምት ሆኖብኛል። ገና ለገና እስልምና ከውጭ የመጣ እምነት ተብሏል እና ክርስትናም ከውጭ የገባ እምነት መባል አለበት የሚል አደገኛ አካሄድ አይቸበታለሁ። እስልምና ከውጭ ወደ ውስጥ የገባ መሆኑን የእምነት ተከታይ የሆኑት ባይክዱም ክርስትና ግን ወደ ኢትዮጵያ ከውጭ መጣ አዲስ ነው የገባው፣ የሚባል ያይደለም። መንግስታችን ለካ አንዳንዴም ሰባኪ ይሆናልi ኢትዮጵያ ቀድሞውኑ በኪዳነ ልቦና፣ በመቀጠልም በኪዳነ ኦሪት ከዚያም በአዲስ ኪዳን አምለኮተ እግዚአብሔርን ትፈጽም ነበር። እነዚህ ሽግግሮች እንደመንግስት ገለጻ 'ገባ፣ወጣ፣' የሚባል ሳይሆን አስቀድሞ የሚታወቅ፣ የሚጠበቅ ነበር። ለምሳሌ ሰብአ ሰገል ከኢትዮጵያ ተነስተው የጌታን መወለድ አውቀው ቤተልሔም ተገኝተዋል። ማን ነገራችው? አስቀድመው የእርሱን መወለድ ሱባኤ ቆጥረው በጸጋ መንፈስ ቅዱስ ተርድተውት ነበርና ጌታ በተወለደ ጊዜ ብሩህ ኮከብ መርቶ ቤተልሔም ድረስ ወስዷቸዋል።ማንም የዓለም ሕዝብ፣ እስራአል እንኳ ሳያውቅ እነርሱ ግን ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነው ያውቁ ነበር። ያ ብቻ አይደለም እንደሚሰቀል፣ እንደሚሞት፣ እንደሚነሳ ይጠባበቁት ነበር። (ወርቅ ለዘላለም መንግስቱ ፣ እጣን ለአምላክነቱ ፣ ከርቤ ለሞቱ ምሳሌ እጅ መንሻ ሰጥተውት ነበረና) ። ለዚያም ነው ሐዋርያው ፊልጶስ ኢትዮጵያዊውን ጃንደረባ ለማጥመቅ እና ለማስረዳት ጊዜ ያለፈጀበት። እንግዲህ ሐዋርያት እንኳ እስራኤልን ተዟዙረው አስተምረው ሳይጨርሱ ገና በአገልግሎት እየተጉ ሳለ ነው ኢትዮጵያዊው ጅንደረባ በ 34 አ.ም. ክርስትናን ይፋ ያደረገው። ይህም የየምስራች ቃል ነው እንጂ አዲስ ሃይማኖት እንደሚገባ ያለ አስተምህሮ አልነበረም። ቃልበቃል ልንረዳው ብንሞክር እንዲህ የሚል ይሆናል 'የኛ ተስፋችን የሆነው ፣ የተወለደው ጌታችን እነሆ ተስፋውን ፈጸመ። ሞትን በሞቱ ድል ነስቶ መንግስተ ሰማያትን አቀረበልን። የተስፋው ቃል ተፈጸመ። ' የሚል ይሆናል። ብቻ ብዙ፣ እጅግ ብዙ ስህተቶችን ተመልክቻለሁ። መንግስት ይህንን የሚያደርገው ሆነ ብሎ ስለሆነ፣ ከስህተቱ ይመለሳል የሚል ግምት የለኝም። ነገር ግን ብዙ ውሸት ሲደጋገም እውነት እንዳይመሰለን የበኩሌን ይህን ብያለሁ። 

ኢትዮጵያ ታበጽ እደዊሃ ሃበ እግዚአብሔር!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ተቃዋሚዎች