ብዙ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ክፍል 1. "ትውልዱ"

24/04/2006

''ብዙ ውሸት ሲደጋገም እውነት ይመስላል'' ለሚለው ብሂል አይነተኛ ምሳሌ ያገኘሁለት ፈረንጆቹ ያከበሩት ያለፈው '' አዲስ ዓመት'' መግቢያ አካባቢ ነው፡፡ ይኸው የፈረደበት ''facebook'' በመልካም ምኞት መግለጫዎች ተጥለቅልቆ ነው የዋለው። በተለይ '' ኢትዮጵያውያን'' የሆኑት ጓደኞቼ! እኛ ኢትዮጵያውያን የራሳችን የሆነ ማንነት፣ ባህል እና ታሪክ ያለን ህዝቦች ነን፡፡ ዛሬ ''በስልጣኔ'' ወደኋላ ብትቀርም ፤ አንድ ወቅት በስልጣኔ ገናናነቷ የምትታወቅ ሀገር መሆኗን ዓለም እራሱ ሊያስተሃቅረው የማይችል ሀቅ ነው። ማን ያውቃል ነገ ደግሞ ዛሬ ሃያላን ነን የሚሉት ሃገራት ወድቀው ድሃ የተባሉት የተናቁት ሃገራት ደግሞ የሚነሱበት ጊዜ ይመጣ ይሆናል። በዚህ መነሳትና መውደቅ ውስጥ ታዲያ አንድን ሀገር ፣ ሀገር ሊያሰኙት የሚችሉት ፤ ታሪክ ፣ ማንነትና ባህል አብረው የሚጓዙ የሀገራት ህልውና ናቸው። እንደምረዳው ደግሞ ማንነት ፣ ባህል እና ታሪክ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችለው ያለው ትውልድ ማንነቱን ባህሉን እና ታሪኩን አክብሮ ሲይዘው አና ሲኖርበት ነው። ባህላችንን የማናከብር ፣ ማንነታችንን የማንጠብቅ ፣ በታሪካችን የማንኮራ ከሆነ ከኛ ለሚቀበለው ትውልድ ባህል ማንነት አና ታሪክ እቁብ የሚገቡ ነገሮች አይደሉም። ለርሱ ባህል ፣ ማንነት እና ታሪክ ሌላውን (ባእዱን) መከተል ብቻ ይሆናል። በየተሌቪዥን መስኮቱ የሚያየውን የነጮች ባህል ባህሉ ፣ ማንነት ማንነቱ እና ታሪክ ታሪኩ አድርጎ ይወስዳል። ይህ ትውልድ እነሆ ተፈጥሯል። የቤቶቻቸው ግድግዳዎች በነጮች ዘፋኞች እና የፊልም አክተሮች የተሞሉ ''ኢትዮጵያዉያን'' ፤ በየመገናኛ ብዙሃኑም እንዲሁ ስለነዚህ ዘፋኞች እና የፊልም አክተሮች የህይወት ታሪክ እና ዝና እስኪበቃው ይጠጡታል። ከዚህም አልፎ ያገር ውስጥ ዘፋኞች እና የፊልም ሰሪዎች የነጮቹን መንፈስ ተዋህደው እንደነሱ ለብሰው ፣ እንደነሱ እየተወዛወዙ ፣ እንደነሱ እየተወኑ የልብህን አደረስንልህ ይሉታል። ዛሬ ዛሬ በየመንገዱ መሳሳም ፣ ወጣቶች እና ተማሪዎች በጭፈራ እና በፈንጠዝያ ማምሸት እና ማደር (ቤተሰብ አውቅና ሰጥቶት ጭምር) አዲሱ ባህላችን እየሆነ መጥቷል። ፊልም ተብየዎቹም ይህንኑ ጸያፍ የዝሙት ምግባር ትውልዱን ''እናዝናናበታለን'' ፣ ''እናጫውትበታለን'' ብለው በግልጥ ሲተገብሩት ይታያሉ። እንዲህ አይነቱ ትውልድ ታዲያ የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ሊያከብር ቢነሳ አይደንቀኝም። ይልቅስ የሚደንቀኝ ፤ ፈረንጆቹ የኛን የቀን አቆጣጠር ትክክለኛ መሆኑን ለመቀበል ዳር ዳር ሲሉ ፣ የኛዎቹ ''ኢትዮጵያዉያን'' የፈረንጆቹን አዲስ ዓመት ከነ ባህላቸው ጭምር ወርሰን ስንገኝ ያኔ ነው የሚደንቀኝ።

ፖፕ ቤኔዲክት 16ተኛ ''Jesus of Nazareth. The infancy narratives'' በተሰኘው መጽሐፋቸው '' እየሱስ ክርስቶስ ተወለደ ብለን ከምናስበው ቀን ቀደም ብሎ ሳይወለድ አይቀርም'' በማለት ትክክለኛውን የቀን አቆጣጠር ለመጠቆም ጥረት አድረገዋል ። ይህንኑ እምነታቸዉንም በማጠናከር በአንድ ካቶሊካዊ መነኩሴ የቀን አቆጣጠር ስሌት ስህተት ምክንያት የቀን አቆጣጠሩ ከነስህተቱ እስካለነበት ጊዜ ድረስ እውነት መስሎ እንደቀጠለ ይገልጻሉ። ክርስቶስ ሲወለድ አመተፍዳ ተጠናቆ አመተ ምህረት የመጣበት ስሰለሆነ ይህንኑ ምክንያት አድረጋ ከክርስቶስ መወለድ ጋር ተያይዞ የቀን አቆጣጠሯን የቀየረች ብቸኛ ሀገር ደግሞ ኢትዮጵያ ናት ። ይህም በየታሪክ ድርሳናቱ ተመዝግቦ የሚገኝ ፤ የጽሁፍም ፣ የትዉፊትም መረጃ ያላት ሀገር ናት። ታዲያ በዘመናችን ያለው ትውልድ እውነቱን ሳይሆን ሲደጋገም እውነት የሚመስለዉን ውሸት ተቀብሎ ''ፈረስ አጎቴ'' አይነት አላዋቂ ሕይወት ሲመራ ያሳዝናል ፣ ያስቆጫል ፣ ያበሳጫልም። ለኔ ኢትዮጵያዊ ፤ ታሪኩን የሚያውቅ ፣ ባህሉን የሚያከብር ፣ በማንነቱ የሚኖር ነው ለኔ ። እኔ የማውቀው ኢትዮጵያዊ እውነት ነው። የእውነት አንድነት ፣ የእውነት ሃይማኖት ፣ የእዉነት የሀገር ፍቅር ፣ የእውነት የሰው ፍቅር ፤ ቅድስት ሀገር የእዉነት ፣ የእውነት ልምላሜ ፣ የእውነት ምግብ ፣ የእውነት መጠጥ ፣ የእውነት........... የእውነት ነበረ ። ዛሬ ትውልዱ በአንድ መስመር ''ሥልጣኔ'' የመሰለውን ድንቁርና መርጦ ደንዝዞ ይገኛል። እነሆ ጭልጥ ባለ የድንቁርና እና የዝቅጠት እንቅልፍ አንቀላፍቷል። በነቃ!!!

አስተያየቶች

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ተቃዋሚዎች

ብዙ ውሽት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ። ክፍል 2 '' መንግስት''