ተቃዋሚዎች


ቅዱስ ጳውሎስ በኤፌ 4:5 " አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት።" ይላል። በዚህ አገላለፁ ቅዱስ ጳውሎስ እየነገረን ያለው የሃይማኖትን አንድነት (አንድ መሆኗን) አንጂ መብዛት እና መለያየት አይደለም። ለመሆኑ የቤተክርስቲያን አንድነት መቼ ተናጋ?
በ257 አ.ም አርዮስ የተባለ መናፍቅ "ወልድ ፍጡር ነው።" የሚል የክህደት ትምህርቱን መንዛት ጀመረ። ይህ ሰው በወቅቱ በነበሩት ጳጳስ (ተፍፃሜተ ሰማዕት) ቅዱስ ጳውሎስ ተወግዞ ከቤተክርስቲያን አንድነት እንዲለይ ተደርጓል። ነገር ግን አኪላስ በተባለ አባት ከግዝቱ ተፈትቶ ከቤተክርስቲያን አንድነት ስለተጨመረ፣ የአርዮስ ክህደት አደባባይ መውጣት ጀመረ። አኪላስም ቀድሞ ግዝቱን እንዳይፈታ ከመምህሩ ቅዱስ ጳውሎስ ተነግሮት የነበረውን ቃሉን ሽሮ ዉግዘቱን በማንሳቱ ተቀስፎ ሞተ።
ይህ የአርዮስ የክህደት ትምህርት ስር እየሰደደ በመምጣቱ በ325 አ.ም በንጉሥ ቁስጠንጢኖስ ዘመን ኒቂያ በተባለች ቦታ ላይ ትልቅ ጉባኤ ተደረገ። በጉባአዉም ላይ 318 ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን አበው ተሰበሰቡ። አርዮስም በጉባኤው ላይ የኑፋዌ ትምህርቱን አሰማ። የትምህርቱም ይዘት ባጭሩ "ውልድ ፍጡር ነው። ነገር ግን ከሌሎች ፍጡር ይበልጣል። ለአብ ፍጡሩም ልጁም ነው። ኋላም በመዋዕለ ሥጋዌ ባሳየው ታዛዥነትና የተጋድሎ ፅናት ከእግዚአብሔር ቡራኬና ፀጋን ተቀብሎ አንደ ፃድቃን እንደ ሰማዕታት ሱታፌ አምላክነትን አገኘ።" የሚል ነው። ይህንንም የክህደት ትምህርት ያለምንም ማፈር በጉባኤው አሰማ። ቅዱስ አትናቴዎስ መፅሐፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ፣ ወልድ የአብ ፍጡር ሳይሆን ራሱ የፍጥረት ባለቤት መሆኑን፣እንደ አባቱ የስግደት እና የአምልኮ ባለቤት መሆኑን እና ሰውም ቢሆን ከአምላክነቱ የጎደለበት እንደሌለ በስፋትና በጥልቀት መፅሐፍ ቅዱስን እያጣቀሰ አፉን አስያዘው።
ጉባኤውም የቅዱስ አትናቴዎስን ትምህርት በመቀበል አርዮስ ከክህደቱ እንዲመለስ ጠየቀው። አርዮስም በክህደቱ ፀና። ከዚህም የተነሳ ቤተክርስቲያን አርዮስን አውግዛ ሐዋርያዊት ጉዞዋን በአንድነት ቀጠለች። ከአርዮስ ቀጥሎ መቅዶንዮስ የተባለ መናፍቅ መንፈስ ቅዱስ ሕጹጽ (ፍጡር) ነው። አካል የለውም ብሎ ማስተማር ጀመረ። በዚህም ጊዜ በ318 አ.ም በቁስጥንጥንያ 150 የሚያክሉ ከዓለም አብያተክርስቲያን የመጡ ሊቃውንት በጉባኤው ላይ ታደሙ። እርሱም እንደግብር አባቱ አርዮስ ከክህደቱ አልመለስ ቢል አውግዘው ለዩት። ከርሱ ቀጥሎ ንስጥሮስ "እየሱስ ክርስቶስ ሁለት አካል ሁለት ባሕሪ ነው። ከማርያም የተወለደው እሩቅ ብዕሲ ነው፣ ቃል በጥምቀት በዮርዳኖስ እስኪያድርበት ድረስ ወልደ ማርያም የቃል ማደርያ ለመሆን ተወለደ። ስለዚህ ማርያም ወላዲተ ሰብ እንጂ ወላዲተ አምላክ አትባልም።" የሚል አይን ያወጣ ኑፋቄውን ይዞ ብቅ አለ። የመንበረ ማርቆስ 24ተኛ ፓትርያርክ የነበረው ቅዱስ ቄርሎስ የሐዋርያትን የሰለስቱ ምዕት የተዋህዶ መዶሻ ይዞ ወደ መድረኩ ወጣ። በ431 አ.ም ኤፈሶን በተሰኘው ከተማ 200 የሚያክሉ ሊቃነ ጳጳሳት ከተለያትዮ አለማት ተጠርተው ጉባኤ ተደረገ። ንስጥሮስ በቤተክርስቲያን ላይ የተከለውን የኑፋቄ ሚስማር ፣ የታወቀው የተዋህዶ አናጺ ቄርሎስ በተዋህዶ ፋስ ፈንቅሎ አወጣው። ጉባኤውም ክርስቶስ አንድ አካል፣ አንድ ባህርይ መሆኑን፣ እመብርሃን ወላዲተ አምላክ መሆኗን መስክሮ፣ ንስጥሮስንና ትምህርቱን አውግዞ ተበተነ።
ነገር ግን በ451 አ.ም ፓፓ ሊዮን በቅዱስ ቄርሎስ ተዋህዶአዊ ትምህርት ግብዓተ መሬት የተፈፀመለት የንስጥሮስን ክህደት የተቀበረበትን አፈር ምሶ በማውጣት ሕይወት ዘርቶበት በኬልቄዶን ጉባኤ ላይ አቆመው። የተዋህዶ አርበኞች "አንገታችንን ለሰይፍ እንሰጣልኝ እንጂ በአባታችን በቄርሎስ የተወገዘውን የክህደት ትምህርት አንቀበልም። " ብለው ከጉባኤው ውጥተው ሄዱ ።ፓፓ ሊዮን በነገሥታቱ ታጅቦና ከርሱ ወገን አሰልፎ ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያንን በሰይፍም በገንዘብም በድለላም ሊያጠፋ ብዙ ጣረ። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ የምሥራቅና የምዕራብ ቤተክርስቲያን ተብሎ በሁለት ጎራ ተከፈለ። በወቅቱ የነበረችው የሮም ንግስት ብርክልያ የእስክንድርያውን ዲዮስቆሮስ የሐዋርያትን እምነት በመመስከሩ፣ "እኛ የጠራነውን ስብሰባ ንቀህ እኛ ባልነው ሁሉ ይስልተስማማሃው ለምንድን ነው?" ብላ ፅሕሙን አስነጨችው። ጥርሱም እስኪረግፍ ድረስ አስደበደበችው። የተነጨ ፅሕሙን እና የረገፈ ጥርሱን በአንድነት አድርጎ ለስክንድርያ ክርስቲያኖች "ንሱ የሃይማኖት ፍሬ" ብሎ ላከላቸው። ይህም ጉባኤ " ጉባኤ ከለባት ውይም ጉባኤ አብዳን" ተብሎ ይታወቃል። የውሾች ጉባኤ እንደማለት ነው። ምክንያቱም የነገስታቱን ፍላጎት ለማሟላት ብቻ የተደረገ ጉባኤ ነበርና ነው። ሮም በስሯ ያሉትን ጠቅላላ ካቶሊካዊ ብላ ጠራች፣ ትርጉሙም የሁሉም ማለት ነው።
ከዚህ ጊዜ በኋላ የምዕራቡን የክርስትና እምነት የሚከፋፍል ሃስብ ደግሞ በ16ተኛው ክፍለ ዘመን ብቅ አለ። ማርቲን ሉተር፤ ዮሐንስ የተባለ መነኩሴ ለህዝቡ በገንዝብ የኃጢያትን ስርየት ሲሸጥ አይቶ በመቃወም በግልፅ ማውገዝ ጀመረ። በ1517 እ.አ ዘጠና አምስቱ አረፍተ ነገሮች (the ninety-five these) በዊተንበርግ ቤተክርስቲያን በር ላይ በወረቀት አድርጎ ለጠፈ። ሉተር በካቶሊክ መነኩሴ የኃጢያት ሥራ የተነሳ ምንኩስና አስፈላጊ እንዳልሆነ፣ ገዳማት መዘጋት እንዳለባቸው፣ በፀሎት ጊዜ የቅዱሳንን ስም መጥራት፣ እነሱን አማላጅ አድርጎ መውሰድ ስህተት መሆኑን እና ማንኛውም ሰው በራሱ አተረጓጎም መጽሐፍ ቅዱስን መተርጎም ይችላል ውደ ሚል ጭልጥ ይወዳለ ስህተታዊ ትምህርቶችን ይዞ መውጣት ጀመረ። በዚህም የፕሮቴስታንት (ተቃዋሚዎች) ሃይማኖት ተፈጠረ። እንግዲህ ከላይ እንዳየነው ከአንዲቷ እናት ቤተክርስቲያን እንዴት አፈንግጠው እንደወጡና አካሄዳቸው ምን እንደሚመስል ለማየት ሞክረናል። ታዲያ እንዲህ እንዲህ እያለ ዛሬ እምነት የሌሽ (atheists) የሞሉበት ትውልድ አፍርተዋል። የዲያቢሎስ ስውሩ አላማ እርሱ ነውና። ከእናት ቤተክርስቲያን የማስኮብለሉ አላማ ወይም ግቡ መጨረሻል ላይ የተፈጠረው ኢ -አማኝ (atheists) ትውልድ ሆኖ እናገኘዋለን።
ዛሬም ብዙዎች ይህችን ሐዋርያዊት ቤተክርስቲያን እጣ ፈንታ እንደ ምዕራባውያኑ ቤተክርስቲያን ፍፁም ፕሮቴስታንታዊ (ተቃዋሚ) ለማድረግ ሲጥሩ ይታያሉ። እነዚህ የጥፋት ኃይሎች በተለይም ቤተክርስቲያኗ ፍፁም ፕሮቴስታንታዊ ገፅ እና አካሄድ እንዲኖራት ብቻ ሳይሆን አስተምህሮዋ እና ማንነቷ ጭምር እንዲቀየር የሚሰሩ ኃይሎች ናቸው። በአጠቃላይ ቤተክርስቲያኗ አርጅታለች ስለዚህ እናድሳት ብለው የተነሱ የዲያቢሎስ የግብር ልጆች ናችው። እምነት አንድ እንጂ የሚቀየር፣ የሚታደስ፣ የሚሻሻል፣ የሚለወጥ አይደለም። በእድሜ ብዛት ያረጁትን ህንፃ ቤተክርስቲያን ቢሆን ለማደስ የተነሱት እሰየው፣ ይበል፣ይበል ያሰኝ ነበር። ግን ይሄ አይሆንም። የግብር አባታቸው ይህን በጎ በጎውን አይፈቅደላችውም። ይባሱኑ የቤተክርስቲያኗን ለዘመናት የፀናውን ስርዓቷን ፣ ዶግማዋን ፣ ቅኖናዋን ለመለውጥ እና ዛሬ ሰዶማውያንን ያፈራውን፤ ባዶውን የቀረውን፤ ለራሳቸው እንኳ መሆን ያቃታቸውን የምዕራባውያኑን (አውሮፓውያውያንን) አስተምህሮ እና አካሄድ ለመትከል ሲጥሩ ይታያሉ። የዋኋን ምእመናን፣ ይህ ስውር ሴራ ያልገባቸው (ያለተገለፀላቸው) ከተሃድሶአውያን ጋር ሲያብሩና ሲተባበሩ ይታያሉ። በተለይም ሆን ተብሎ የቤተክርስቲያኗን ሀብት የሆነውን፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት በቅዱሳን አባቶች ደራሲነት ለዘመናት ስትጠቀምበት የኖረችውን ያሬዳዊ ዜማ በዘፈን ዜማና ግጥማቸው ከአውሮፓዉያኑ ጋር አንድ ለመሆን ያደርጉት ጥረት ከፍ ያለ ነው። የተሃድሶአውያኑ አላማም ቀስ በቀስ ምዕመናን የቤተክርስቲያን ስርአቷን እንዲጥሱ እራሳችው ተሃድሶአውያኑ እየጣሱ ማሳየት፤ በስነ-ጥበብ ስም በየቲያትር ቤቱ፣ በሚፅፉት መፃህፍት እንዲሁም በየመገናኛ ብዙሃኑ ጭምር ጎራ ሳይለይ ቤተክርስቲያኗን የሚያንቁአሽሽ፣ የሚያናንቅ፣ የሚተች እና የሚያወግዝ ስራዎች በሰፊው በመስራት የራሷ የቤተከርስቲያኗ ምዕመናን ቤተክርስትያኗን እንዲጠራጠር እና ቤተከርስትያን ላይ ፊቱን እንዲያዞር ማድረግ ነው።ለዚህ ነው የዋኋን ምእመናን በተሃድሶ እንቅስቃሴ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መጠበቅ አለባቸው የምንለው።
ዛሬ "እየሱስን ተቀበል" እያሉ በየመንገዱ የሚዞሩትን ኢትዮጵያውያን ተቃዋሚዎች (ፕሮቴስታንት) የእምነታቸው መስራች የሆነችው አገር ጀርመን በእምነት የለሽ (atheist) ብዛት ከጠቅላላው ሕዝብ ብዛት ወደ 34% ያህሉን ሲይዝ፣ ፕሮቴስታንት ደግሞ 29.8% ብቻ መሆኑን ማን በነገራቸው።ይህ እንግዲህ የተቃዋሚዎች ፍሬ ነው። ማቴ 2፣16 "ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ።" እንዳለ መፅሐፍ።እንግዲህ አብዘሀኛው የጀርመን ክፍል እምነት የለሽ ሆኖ ሳለ፤ መሰበክ፣ መመከር፣ መገሰፅ የሚገባው እራሳቸው ያፈሯቸው የራሰቸው አገር ሰዎች ሆኖ ሳለ፣ በእምነቷ ፀንታ የምትኖርን ሀገር ክርስቶስን ተቀበይ ብሎ መሞገት የጤና እንዳልሆነ ለመረዳት አያዳግትም። የኛዎቹን በየመንደሩ የሚዞሩትን ተቃዋሚዎች ቀለብ ሰፍረው እንዲዞሩ ሲያደርጉ፣ ዝም ብልን ማየት አለብን ብዬ አላስብም።ባለማወቅ ከሆነ ቤተክርስቲያንን ልናሳያቸው፣ ስለእምነት ልናስተምራቸው፣ የአዋቂ አጥፊ ከሆኑ ደግሞ ልናዝንላቸው፣ ልንለምንላቸው ይገባል ባይ ነኝ።
ቤተክርስቲያኗ ለዘመናት ስትገለገልባቸው የቆዩትን መንፈሳዊ ሀብቷን ለማስጣልና አውሮፓዊ ለማድረግ አሁንም ጥረቱ ቀጥሏል። በገናዋን በአርጋን፤ ቅዳሴዋን "በልሳን"፤ ዝማሬዋን በዘፈን ለመቀየር ሌት ከቀን ይሰራሉ። የቅድስት ቤተክርስቲያን ምዕመናን ይህንን የረቀቀ የዲያቢሎስ ስራ አውቀውና ነቅተው ቤተክርስቲያናቸውን መጠበቅ አለባቸው። እንደ ትውልድም የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣት አለብን።አባቶቻችን ዳዋ ጥሰው፣ ጤዛ ልሰው፣ ድንጋይ ተንተርሰው፤ ደረታቸውን ለጦር፣ እግራቸውን ለጠጠር ሰጥተው፤ ሰማዕታት ደማቸውን አፍስሰው ያቆዩልንን ቤተክርስቲያናችንን እንደ አይን ብሌናችን ልንጠብቃት ይገባል።ተሃድሶአውያኑንም ከተመለሱ በፍቅር ፣ በምክር፤ ካልተመለሱ ግን ተወግዘው መለየት አለባቸው። የዉኋን ምእመናንን የበግ ለምድ ለብሰው እንዳይነጥቁ ለምዱ ተነጥቆ ተኩላዉ መለየት አለበት። ሮሜ 7፣ 15-23 " ነገር ግን ወንድሞች ሆይ፣ እናንተ የተማራችሁትን ትምህርት የሚቃወሙትን መለየትና ማሰናከያ የሚያደርጉትን ሰዎች እንዳትመለከቱ እለምናቹኋለሁ። ከእነርሱ ዘንድ ፈቀቅ በሉ። እንዲህ ያሉት ለገዛ ሆዳቸው እንጂ ለጌታችን ለእየሱስ ክርስቶስ አይገዙም እና በመልካም እና በሚያቆላምጥ ንግግር ተንኮል የሌላቸውን ሰዎች ልብ ያታልላሉ።" እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ።
ይቆየን

አስተያየቶች

አስተያየት ይለጥፉ

ከዚህ ጦማር ታዋቂ ልጥፎች

ብዙ ውሽት ሲደጋገም እውነት ይመስላል ። ክፍል 2 '' መንግስት''